Proverbs 19

1ንግግሩ ጠማማ ከሆነ ዐጕል ሰው ይልቅ፣
ያለ ነውር የሚሄድ ድኻ ሰው ይሻላል።

2ዕውቀት አልባ የሆነ ቀናኢነት መልካም አይደለም፤
ጥድፊያም መንገድን ያስታል።

3ሰው በራሱ ተላላነት ሕይወቱን ያበላሻል፤
በልቡ ግን እግዚአብሔርን ያማርራል።

4ሀብት ብዙ ወዳጅ ታፈራለች፤
ድኻን ግን ወዳጁ ገሸሽ ያደርገዋል።

5ሐሰተኛ ምስክር ከቅጣት አያመልጥም፤
ውሸት የሚነዛም ሳይቀጣ አይቀርም።

6ብዙ ሰዎች በገዥ ዘንድ ሞገስ ለማግኘት ያሸረግዳሉ፤
ስጦታን ከሚሰጥ ሰው ጋር ሁሉም ወዳጅ ነው።

7ድኻ በሥጋ ዘመዶቹ ሁሉ የተጠላ ነው፤
ታዲያ ወዳጆቹማ የቱን ያህል ይሸሹት!
እየተከታተለ ቢለማመጣቸውም፣
ከቶ አያገኛቸውም።
ለዚህ ዐረፍተ ነገር የገባው የዕብራይስጡ ትርጓሜ በትክክል አይታወቅም።


8ጥበብን ገንዘቡ የሚያደርጋት ነፍሱን ይወድዳል፤
ማስተዋልን የሚወድዳት ይሳካለታል።

9ሐሰተኛ ምስክር ከቅጣት አያመልጥም፤
ውሸት የሚነዛም ይጠፋል።

10ተላላ ተንደላቅቆ መኖር አይገባውም፤
ባሪያ የመሳፍንት ገዥ ከሆነማ የቱን ያህል ይከፋ!

11ጥበብ ሰውን ታጋሽ ታደርገዋለች፤
በደልን ንቆ መተውም መከበሪያው ነው።

12የንጉሥ ቍጣ እንደ አንበሳ ግሣት ነው፤
በፊቱ ሞገስ ማግኘትም በሣር ላይ እንዳለ ጠል ነው።

13ተላላ ልጅ ለአባቱ መጥፊያ ነው፤
ጨቅጫቃ ሚስትም እንደማያቋርጥ ጠፈጠፍ ናት።

14ቤትና ሀብት ከወላጆች ይወረሳሉ፤
አስተዋይ ሚስት ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ ናት።

15ስንፍና ከባድ እንቅልፍ ላይ ይጥላል፤
ዋልጌም ሰው ይራባል።

16ትእዛዞችን የሚያከብር ሕይወቱን ይጠብቃል፤
መንገዱን የሚንቅ ግን ይሞታል።

17ለድኻ የሚራራ ለእግዚአብሔር ያበድራል፤
ስላደረገውም ተግባር ዋጋ ይከፍለዋል።

18ገና ተስፋ ሳለ፣ ልጅህን ሥርዐት አስይዘው፤
ሲሞት ዝም ብለህ አትየው።

19ግልፍተኛ ሰው ቅጣትን መቀበል ይገባዋል፤
በምሕረት ካለፍኸው ሌላም ጊዜ አይቀርልህም።

20ምክርን ስማ፤ ተግሣጽን ተቀበል፤
በመጨረሻም ጠቢብ ትሆናለህ።

21በሰው ልብ ብዙ ሐሳብ አለ፤
የሚፈጸመው ግን የእግዚአብሔር ሐሳብ ነው።

22ሰው የሚመኘው ጽኑ ፍቅር
ወይም የሰው ሥሥት ውርደት ወይም ኀፍረት ያመጣበታል።
ነው፤
ውሸታም ከመሆንም ድኻ መሆን ይሻላል።

23 እግዚአብሔርን መፍራት ወደ ሕይወት ይመራል፤
እንዲህ ያለውም ሰው እፎይ ብሎ ያርፋል፤ መከራም አያገኘውም።

24ሰነፍ እጁን ከወጭቱ ያጠልቃል፤
ወደ አፉ ግን መመለስ እንኳ ይሳነዋል።

25ፌዘኛን ግረፈው፤ ብስለት የሌለውም ማስተዋልን ይማራል፤
አስተዋይን ዝለፈው፤ ዕውቀትን ይገበያል።

26አባቱን የሚዘርፍ፣ እናቱንም የሚያሳድድ፣
ዕፍረትና ውርደት የሚያመጣ ልጅ ነው።

27ልጄ ሆይ፤ እስቲ ምክርን ማዳመጥ ተው፤
ከዕውቀትም ቃል ትስታለህ።

28አባይ ምስክር በፍትሕ ላይ ያፌዛል፤
የክፉዎችም አፍ በደልን ይሰለቅጣል።

29ለፌዘኞች ቅጣት፣
ለተላሎችም ጀርባ ጅራፍ ተዘጋጅቷል።
Copyright information for AmhNASV